*Announcement* Anbesa Bank has officially rebranded It's Identity.

የአንበሳ ባንክ የአዲሱ ብራንድ ምረቃ መርሃ ግብር ብራንዱን በጥልቀት በሚተርኩ ልዩ ልዩ መሰናዶዎች በደማቅ ሁኔታ ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም በአድዋ ሙዚየም ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ በሚኒስትር ማዕረግ በምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ክቡር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማት ሱፐርቪዥን ምክትል ገዢ ክቡር አቶ ሰለሞን ደስታ፣ የብሔራዊ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ገዢ ክቡር አቶ ኢዮብ ገ/ኢየሱስ፣ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የባንኩ ደንበኞች፣ የባንኮች ዋና ስራ አስፈጻሚዎች፣ የባንኩ አጋሮች፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች፣ የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት፣ የባንኩ ፕሬዚደንት፣ የስራ አስፈጻሚ አባላት፣ የስራ ኃላፊዎች እና ሰራተኞች እንዲሁም በርካታ ጥሪ የተደረገላቸው ባለድርሻ አካላት በክብር እንግድነት ተገኝተው ነበር፡፡

ወደ ብራንድ ምረቃ መርሃ ግብሩ የተጠሩ እንግዶች ሲገቡ ‘ምን እንደማስብ ታውቃላችሁ?’ የሚለውን የቲዘር መልዕክት የሚያሳዩ ባነሮች፣ የብራንዱን ቀለም በለበሱ አበባዎች፣ የብራንዱን መልዕክት የሚያሳዩ ስክሪኖች፣ ለፎቶ መነሻ የተዘጋጁ ባነሮች፣ ሰርከስ በሚሰሩ ወጣቶች ትዕይንት እንዲሁም ብራንዱን በሚወክል የአገር ባህል ልብስ በደመቁ የአንበሳ ባንክ የስራ አመራር አባላት አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

አዲሱ ብራንድ የሚመረቅበት አዳራሽም እንዲሁ ዘመናዊ የሆነ መድረክ ተገንብቶ በግዙፍ ስክሪን በሚተላለፉ መሳጭ መልዕክቶች ተውቦ ነበር እንግዶችን ያስተናገደው፡፡ ቫዮሊን፣ ክራር፣ ሳክስፎን፣ ከበሮ እና ሌሎች መሳሪያዎችን የሚጫወቱ ሙዚቀኞች አገራዊ ዜማዎችን በማሰማት ለኹነቱ ልዩ ድባብ ፈጥረው ነበር፡፡

ሁሉም እንግዶች በመቆም የኢትዮጵያ በብሔራዊ መዝሙርን በማዜም መርሃ ግቡሩን የከፈቱ ሲሆን የአንበሳ ባንክ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለም አስፋው እና የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ዳንኤል ተከስተ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት እና የመክፈቻ ንግግር እንደየቅደም ተከተላቸው አድርገዋል፡፡ 

የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለም አስፋው እንግዶች የባንኩን ጥሪ አክብረው ከአገር ውስጥም ከአገር ውጭም የመጡ እንግዶችን እና ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን እንደ ፕሮቶኮላቸው እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

አንበሳ ባንክ ብራንዱን በአዲስ መልክ ለመቅረጽ መነሻ የሆነውን ምክንያት በመክፈቻ ንግግራቸው በስፋት የተረኩት የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ዳንኤል ተከስተ ይህ ብራንድ ሲቀረጽ ‘‘ባንካችን አዲስ የነደፈውን ፍኖተ ካርታ ተንተርሶ ሲሆን አንበሳ ባንክ ለቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በኢንደስትሪው ተወዳዳሪ እና ተመራጭ የሚያደረገውን፤ ለደንበኞቹ ብሎም ለሚያገለግለው ህብረተሰብ ትርጉም ያለው የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመኑን የሚዋጅ የዲጂታል አገልግሎት ለማቅረብ የሚያበቃውን፣ በልዩ ልዩ አገልግሎቶቹም ፈጠራን ያማከለ ስራ ለመስራት የሚያስችለውን የስትራቴጂ አቅጣጫ ቀይሷል፡፡’’ ሲሉ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር አውስተዋል፡፡

የባንኩ ዓላማ – ለሀብት መስፋፋት ትርጉም ያለው የፋይናንስ ጠቀሜታ እና እድሎችን መስጠት፤ ራዕዩም – ህልምን የሚያቀጣጠል፣ ትልምን እውን የሚያደርግ እንዲሁም ወደ ግብ የሚደረገውን ጉዞ የሚያበረታ አጋር መሆን፤ ተልዕኮው – በሚያገለግለው ህብረተሰብ ውስጥ ዘላቂ አጋርነት እና የተከበረ የአኗኗር ዘይቤን ለመገንባት የተቀናጁ የፋይናንስ መፍትሄዎችን ማቅረብ እንደሆነ በስትራቴጂ ሰነዱ ተጠቅሷል፡፡ 

ከዚህ ጋር በተያያዘ አቶ ዳንኤል ተከስተ ‘‘ዛሬ (ጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም.) በይፋ ለእናንተ የምናቀርበው ወደ አዲስ ምዕራፍ የምናደርገውን ሽግግር የሚገልፀውን የተለወጠ ብራንድ የቀረጽነው በእነዚህ የአንበሳ ባንክ አዕማዶች ላይ ተመርኩዘን ነው፡፡ ዛሬ የምናስተዋውቃችሁ አዲሱን ሎጎአችንን ወይም ቀለማችንን ወይም መሪ ቃላችንን ወይም ጂንግላችን ብቻ ሳይሆን ባንካችን እስከ አሁን ራሱን ፖዚሽን ያደረገበትን መንገድ የቀየረበትን እና ሙሉ በሙሉ ወደ ለውጥ እየተሻገረ መሆኑን የሚያበስር ማንነታችንን ነው፡፡’’ በማለት የባንኩን ፍኖተ ካርታ እና የብራንድ ለውጡን ቀጥተኛ ግነኙነት ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የብራንዱን ጽንሰ ሃሳብ በተመለከተ ማንኛውንም ጉዞ ለመጀመር የሚያስፈልገው የጭረት ያክል ድፍረት፤ የጠጠር ያክል ድጋፍ ነው ከሚል ጽንሰ ሃሳብ መሆኑ የተነገረ ሲሆን አቶ ዳንኤል በንግግራቸው ‘‘በውስጣችን የሚመላለሱ፣ ስንተኛም ስንነሳም የሚሞግቱን የቢዝነስ ሊሆን ይችላል ወይም ሌሎች ታላላቅ ሃሳቦች፣ ህልሞች፣ ውጥኖች፣ እቅዶች በብዙዎቻችን የአእምሮ ጓዳ ይኖሉ፡፡ እነዚህን ሃሳቦች ለመጀመር የሚያበረታታን ወይም የሚያደፋፍረን የጭረት ያክል ትንሽ ብልጭታ የሚፈጥርልን ወዳጅ ያስፈልገናል፡፡ ይህን ብልጭታ የሚፈነጥቅልን ወይም የሚያስጀምረን አጋር ያስፈልገናል፡፡ በርካታ ትልልቅ ውጤቶች፣ መከናወኖች እና ስኬቶች የተነሱት ከትንሽ ጭረት፤ ከታማኝ አጋር ነው፡፡ እኛም በተልዕኳችን እንዲሁም በራዕያችን እንደገለጽነው በየትኛውም አይነት የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚገኝ ሰው በውስጡ ከሚመላለሱ የለውጥ ሃሳቦች፣ ህልሞች እንዲሁም ባሳካቸው ከሚላቸው ትልሞች ጋር እንዲገናኝ፣ ጉዞውን እንዲጀምር የጭረቷ መነሻ ታማኝ አጋር ነን እያልን ነው፡፡’’ በማለት የብራንዱን ማእከላዊ መልዕክት አቅርበዋል፡፡

ይህ ማዕከላዊ መልዕክት ባንኩ ለደንበኞቹ፣ ለባለአክሲዮኖቹ፣ ለአጋሮቹ፣ ለሚያገለግለው ህብረተሰብ እንዲሁም ለኢንደስትሪው የሚያበስረው የብራንዱ አዲስ አቅጣጫ መሆኑን እና ይህ የብራንዱ እሳቤ በባንኩ አርማ፣ ቀለማት፣ መሪ ቃል፣ መልዕክቶች እንዲሁም ጂንግል ግዝፈት መንሳቱ ተነግሯል፡፡

በዚህ ማዕከላዊ ገዢ ሃሳብ መሰረት ከዚህ በኋላ አንበሳ ባንክ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከዘመኑ ጋር የሚሄዱ፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂ የተቃኙ፣ ደንበኞችን ማዕከል ያደረጉ፣ የመፍትሄ ምንጮች፣ ለህብረተሰቡ የተከበረ የአኗኗር ዘይቤን የሚያላብሱ፣ ለሀብት መስፋፋት አቅም ሚፈጥሩ፣ ህልምን ከግብ የሚያገናኙ እንደሚሆኑ፤ የባንኩም አካሄድ ከተለመደው የተለየ ይሆናል፡፡ ብራንዱም እነዚህኑ የባንኩን የማንነት ዋልታዎች የሚያንጸባርቅ ጊዜውን የዋጀ ሆኖ ሊቀረጽ መቻሉ ተገልጿል፡፡

የብራንድ ምረቃ ስነስርዓቱ ከመድረኩ ላይ በሚተላለፉ ቀልብ የሚስቡ ክዋኔዎች የታጀበ ሲሆን የብራንዱ አዲስ ጂንግል በአርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) እና በህብረ ዝማሬ አባላቱ በመሳጭ የዜማ ቅንጅት ቀርቧል፡፡ ይህን ተከትሎም የታዳሚዎችን ልብ የማረከ የብራንዱ እሳቤዎች መገለጫ የሆኑትን ጥንካሬን፣ ልበ ሙሉነትን፣ ባለራዕይነትን፣ ለመጀመር መነሳትን የሚተርክ የተቀናጀ ዘመናዊ የዳንስ እና ሰርከስ ትርኢት ቀርቧል፡፡

የብራንዱ አብይ አካል የሆነው የአንበሳ ባንክ አርማ ግዙፍ በሆነው ስክሪን ላይ ሲገለጥ አገራዊ ታሪክን፣ ባህልን እና ሥርዓትን ባንጸባረቀ ሁኔታ በነጋሪትና በመለከት ታጅቦ ይፋ ሆኗል፡፡

የአንበሳ ባንክ አዲስ ብራንድ ስያሜውን በእንግሊዝኛ ከተተረጎመው Lion International Bank እንዲሁም በአማርኛ አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ከሚለው መጠሪያ አውጥቶ በሁለቱም ቋንቋዎች አንበሳ ባንክ/anbesa bank የሚልን ስያሜ ብቻ ወስዷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ብራንዱ ካስተዋወቃቸው መገለጫዎች መካከል አዲስ ሎጎ – በክብ ቅርጽ ውስጥ የብርሃን ፍንጣቂ ጭረት፤ ቀለም – ወርቅማ እና ጥቁር፤ መሪ ቃል – እንጀምረው!/LET’s GO FOR IT! ከዚህ ቀደም ያልነበረ – የብራንድ መዝሙር/ጂንግል እንዲሁም የጽሁፍ ፎንቶች ይገኙበታል፡፡
በመድረኩ ላይ ለአዲሱ ብራንድ ስኬት ከጎናችን የነበሩ እና ጉልህ አስተዋፅኦ ለበረከቱ ድርጅቶች እና ግለሰቦች የእውቅና እና የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የአንበሳ ባንክ የብራንድ ምረቃ መርሃ ግብር የተጠናቀቀው ከአዳራሽ ውጭ በተካሄዱ መርሃ ግብሮች ሲሆን ብራንዱን የሚገልጹ ስጦታዎች፣ ብራንዱን በዲጂታል ስክሪን ከቀረቡ ምስሎች ውስጥ ለይቶ የማውጣት ጨዋታዎች፣አንበሳ ባንክ-እንጀምረው የሚሉ ባነሮች፣ የባንኩ ስም እና አርማ የታተመባቸው ወዲያውኑ ታጥበው የሚሰጡ ፎቶግራፎች፣ የሰርከስ ትርኢቶች እና ሌሎችም በርካታ ክዋኔዎች የብራንድ ምረቃ ስነስርዓት ፍጻሜውን አድምቀውት ነበር፡፡
አንበሳ ባንክ
እንጀምረው!

Leave A Comment