*Announcement* Anbesa Bank has officially rebranded It's Identity.

(ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም) አንበሳ ባንክ እ.ኤ.አ የ2025/26 አራተኛ ሩብ ዓመት እና ዓመታዊ የስራ አፈፃፀም አስመልክቶ በተለያዩ የክንውን ጉዳዮች ዙሪያ ሲያደርግ የነበረውን ጉባዔ በዛሬው ዕለት አጠናቋል፡፡

ለተከታታይ ሁለት ቀናት በተከናወነው በዚሁ የስራ አፈፃፀም ስብሰባ በተቀማጭ ገንዘብ፣ በብድር፣ በውጭ ምንዛሪ፣ በዲጂታል ባንክ አገልግሎት፣ በወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት፣ በደንበኛ አገልግሎት እንዲሁም በሌሎች የስራ ክንውኖች ዙሪያ የእቅድ እና አፈጻጸም ሪፖርቶች ላይ ሰፊና ጠለቅ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡

ሁሉም የስብሰባው ታዳሚዎች በእቅድ እና አፈፃፀም ዙሪያ በቀረቡ ሪፖርቶች ላይ የነቃ ተሳትፎ ያደረጉ ሲሆን ደካማ ጎኖችን በማሻሻል በቀጣይ የተሻለ ውጤት በማስመዝገብ ባንኩን ወደላቀ ከፍታ ማብቃት ላይ ያላቸውን አቅም ሁሉ አሟጠው እንደሚጠቀሙ ቃል ገብተዋል፡፡

የባንኩ ፕሬዝደንት አቶ ዳንኤል ተከስተ በቀረቡ ሪፖርቶች እና ውይይቶች ላይ አንኳር ነጥቦችን በማንሳት ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ማጎልበት እንዲሁም ዝቅተኛ አፈፃፀሞችን በቁርጠኝነት እና በጽናት ማረቅ ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን ገልፀው ባንኩ በቀጣይ በጀት ዓመት ደንበኛ ተኮር የባንክ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት በአፅንዖት ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም በባንኩ የሶስት ዓመት ፍኖተ ካርታ መሰረት 2026/27 የስራ ዘመን ዕቅድ እና በጀት ቀርቦ ሁለንተናዊ ውይይት የተካሄደበት ሲሆን ይህ አዲስ ዕቅድ ባንኩን ወደ ታለመለት ግብ አና አመርቂ እድገት ለማድረስ ጥርት ያለ አቅጣጫ ማስቀመጡ ተወስቷል፡፡

በበጀት ዓመቱ የላቀ አፈፃፀም ያመጡ ዲስትሪክቶች ዕውቅና የተቸራቸው ሲሆን የምስክር ወረቀት እና ሽልማት ከባንኩ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለም አስፋው፣ ከባንኩ ፕሬዝደንት አቶ ዳንኤል ተከስተ እንዲሁም ከሪቴል ባንክ ም/ፕሬዚደንት አቶ ሚካኤል ገዛኢ እጅ ተቀብለዋል።

በመጨረሻም የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለም አስፋው በስብሰባው ላይ በመገኘት በርካታ ተግዳሮቶችን በመቋቋም ከፍተኛ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ዲስትሪክቶች ምስጋና ሲያቀርቡ በቀጣይ በጀት ዓመት ሁሉም የባንኩ አካላት በጠንካራ መንፈስ ለተሻለ አፈፃፀም መትጋት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

አንበሳ ባንክ
እንጀምረው!

Leave A Comment