(መስከረም 06 ቀን 2019 ዓ.ም.) አንበሳ ባንክ ወደ ሥራ ባስገባው የሶሰት ዓመት ዕቅዱ መሰረት ልዩ ልዩ ጥቅሞችን ያካተቱ የባንክ አገልግሎቶችን ለዲያስፖራው ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ የቀረጸውን ጥቅል አገልግሎት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ተከስተ በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት በተዘጋጀ መርሃ ግብር ላይ በዛሬው ዕለት ይፋ አድርገዋል፡፡
ይህ በአይነቱ ልዩ የሆነ የዲያስፖራ ጥቅል አገልግሎት ባንኩ በቅርቡ ወደ ትግበራ ከቀየረው ፍኖተ ካርታ አንጻር ልየ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት የሚገኝ ሲሆን ጥቅሉ በሶስት ዋና ዋና ምዕራፎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ መሆኑ በመርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል፡፡
ከዚህም ጋር በተያያዘ በዛሬው ዕለት ይፋ የተደረገው ይህ የጥቅል አገልግሎት የመጀመሪያ ምዕራፍ ሲሆን በቀጣይ የዲያስፖራውን ፍላጎቶች የሚያሟሉ እና ሰፊውን የዲያስፖራ ማህበረሰብ ተደራሽ የሚያደርጉ፣ የዲጂታል አማራጮችን ያካተቱ፣ እንዲሁም በርካታ አገልግሎቶችን ያዘሉ ጥቅሎች ይፋ የሚደረጉ ይሆናል፡፡
ባንኩ ይህን መሰል ጥቅል የባንክ አገልግሎት ከዲያስፖራው ማህበረሰብ ባለፈ ለሰፊው ህብረተሰብ ለማቅረብ የሚያስችለውን ስራ በትጋት እያከናወነ ይገኛል፡፡

Leave A Comment