በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ዳንኤል ተከስተ እና በቫይት ቴክኖሎጂስ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ገ/ኪዳን ገ/መድህን ዛሬ ህዳር 5 ቀን 2016 ዓ.ም በመቐለ ከተማ የተፈረመው ስምምነት የባንኩን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ለማጎልበት እና የክፍያ ስርዓትን በማዘመን ደንበኞች የትምህርት ቤት፣ የውሃ እና የመዘጋጃ ቤት አገልግሎት ክፍያዎችን በኤሌክትሮኒክስ አሰራር መክፈል የሚችሉበትን ስርዓት መዘርጋት እንዲሁም የባንኩን የዳታ አያያዝና የደህንነት ስርዓትን በማጎልበት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነው፡፡
በተጨማሪም በፋይናንስ ዘርፍ የተሰማሩ ማይክሮ ፋይናንስ እና የብድርና ቁጠባ የህብረት ስራ ማህበራት የሚገለገሉባቸውን የክፍያ ቴክኖሎጂዎችን ከባንኩ የኢንፎርሜሽን ቴከኖሎጂ ስርዓት ጋር የማቀናጀት ስራ ይሰራል፡፡ በዚህም መሰረት የብድርና ቁጠባ ማህበራት አባሎች ወደየማህበራቸው የባንክ ሂሳብ ገቢ የሚደረግ ተቀማጭ ገንዘብ በአንበሳ በኢንተርናሽናል ባንክ በኩል ገቢ ለማድረግ የሚያስችላቸውን አሰራር እንደሚፈጠርላቸው ተገልጿል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ቫይት ቴክኖሎጂስ የባንኩን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን የተመለከቱ ጥናቶች በማካሄድ ለባንኩ የማማከር አገልግሎት እንደሚሰጥም ታውቋል፡፡