የአንድ አክሲዮን የትርፍ ድርሻ ብር 423.82 (42.3 በመቶ) ሆኗል
በአሁኑ ሰዓት የባንኩ የተከፈለ ካፒታል ብር 5.8 ቢሊየን ደርሷል
(ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም.) አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በ2017 በጀት ዓመት ከታክስ በፊት 1.8 ቢሊየን ብር ትርፍ ያገኘ ሲሆን አፈጻጸሙም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ94 በመቶ እድገት ማሳየቱ ቅዳሜ ጥቅምት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በሸራተን ሆቴል በተካሄደው የባንኩ 21ኛ መደበኛ እና 7ኛ ድንገተኛ የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተገለጸ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከአንድ አክሲዮን የተገኘ የትርፍ ድርሻ ብር 423.82 ወይም 42.3 በመቶ በመሆን ከፍተኛ እድገት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡
ይህ አመርቂ አፈፃፀም የባንኩን ጥንካሬ አጉልቶ የሚያሳይና ለቀጣይ የላቀ ስኬት መንደርደሪያ እንደሆነ የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ አለም አስፋው የተናገሩ ሲሆን የባንኩን የተከፈለ ካፒታል አቅም ብር 5.8 ቢሊየን በላይ በማድረስ በብሔራዊ ባንክ ከተቀመጠው ዝቅተኛ መስፈርት ከፍ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ባንኩ በበጀት ዓመቱ ስድስት ቢሊየን ብር ብድር የሰጠ ሲሆን ከብድር ክፍያዎች ብር 5.2 ቢሊየን መሰብሰብ ችሏል። በሂሳብ ዓመቱ ማብቂያ ላይ የባንኩ አጠቃላይ የብድር መጠን ብር 36.2 ቢሊየን ሆኖ ሲመዘገብ ባንኩ ኢንቨስት ያደረገበት የግምጃ ቤት ሰነድ እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦንድ ግዥ ብር 4.1 ቢሊየን ደርሷል።
የባንኩ አጠቃላይ ሃብት ብር 54 ቢሊየን ሲደርስ የባንኩ ዕዳ ደግሞ ብር 47.5 ቢልየን ሆኗል። ከዚህ ባሻገር የባንኩ አጠቃላይ የካፒታልና መጠባበቂያ ክምችት ብር 6.5 ቢሊየን ደርሷል። በሀብት ማሰባሰብ ረገድ ባንኩ በበጀት ዓመቱ ብር 8.3 ቢሊየን ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰቡን እና አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን ብር 44 ቢሊየን ማድረስ መቻሉን ሰብሳቢው የገለጹ ሲሆን አፈጻጸሙም ካለፈው ዓመት አንጻር የ25 በመቶ እድገት ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ባንኩ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ እድገት ያለው የውጭ ምንዛሪ ማሰባሰብ መቻሉ ተነግሯል።
በቅርንጫፍ እና በዲጂታል የባንክ አገልግሎት ተደራሽነትን ከማጎልበት አንጻር በርካታ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሰፊ የደንበኞች መሰረት በመፍጠር ባንኩ ከ2.4 ሚሊየን በላይ ደንበኞችን ማፍራት ችሏል፡፡
ከዋስትና ማስያዣ ነጻ በሆነው “አለኝታ” ዲጂታል ብድር ባንኩ ከ5,000 በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን የትምህርት ቤት ክፍያ እና የህብረት ስራ ማህበራት የገንዘብ ልውውጥን የሚያሳልጡ ስርአቶችን ስራ ላይ በማዋል በርካታ ደንበኞችን ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮቴሌኮም፣ ከሳፋሪኮም፣ ከሳንቲም-ፔይ እና ሌሎች የፊንቴክ ኩባንያዎች ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነት በመፍጠር የባንኩን ተደራሽነት ይበልጥ በማስፋት የደንበኞችን ፍላጎት በማሟላት ረገድ ምቹ ተግባራት ተከናውነዋል።
በሂሳብ ዓመቱ ከተከናወኑ ጉልህ ተግባራት አንዱ ‘አል-ነጃሺ’ የተሰኘ የሼሪአ መርሆችን የጠበቀ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መጀመሩ ሲሆን በአሁኑ ሠዓት በትግራይ – መቀሌ፣ በአፋር – ሎጊያ እና በአዲስ አበባ – ቤቴል ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት ብቻ የሚሰጡ ቅርንጫፎች ተከፍተው አገልግሎት ሲሰጡ በሁሉም የባንኩ ቅርንጫፎች ይኽው አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የባንኩ የሰው ሃይል ወደ 6,888 ሲያድግ ከነዚህ መካከል 50% ያህሉ በቋሚ ቅጥር የስራ መደቦች ላይ ይገኛሉ። በበጀት ዓመቱ ብቻ ለ348 አዲስ ሰራተኞች የስራ እድል የተፈጠረ ሲሆን በተለያየ ምክንያት ስራቸውን የሚለቁ ሰዎች ምጣኔ ከ4.5 በመቶ እንዳይበልጥ ማድረግ ተችሏል። በተጨማሪም የሰራተኞችን ክህሎት ለማሳደግ እና ቅልጥፍናቸውን ለማጎልበት በዘርፈ ብዙ የሙያ መስኮች ላይ ያተኮሩ የስልጠና መርሃ ግብሮች ላይ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት ተደርጓል በውጤቱም የተረጋጋ የስራ አካባቢ ለመፍጠር አስችሏል፡፡
አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በህብረተሰቡ ላይ በጎ ተጽዕኖ ለመፍጠር በትጋት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን በበጀት ዓመቱ የተለያዩ የማህበረሰብ ልማት ላይ ያተኮሩ ስራዎችን ለመደገፍ 9.3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል። በተጨማሪም በማህበረሰብ ልማት ዙሪያ ንቁ ተሳትፎ ለሚያደርጉ የሲቪክ ማህበራትና ተቋማት 5.1 ሚሊዮን ብር ስፖንሰር አድርጓል።
አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ
የስኬትዎ አጋር

Leave A Comment