- የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት በአበረታች ውጤት አጠናቋል
———————————————————
(ሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም.) እ.ኤ.አ ሰኔ 30 ቀን 2026 የተጠናቀቀውን በጀት ዓመት በበርካታ ቁልፍ የስራ አፈጻጸም መለኪያዎች አበረታች ውጤት በማስመዝገብ ወደ አዲስ የስራ ዘመን መሸጋገሩን የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ዳንኤል ተከስተ የገለጹ ሲሆን በዚህ አዲስ የስራ ዓመት አዲስ መንገድ፣ አዲስ እቅድ፣ አዲስ ምዕራፍ በመቀየስ ወደ ከፍታ የሚሸጋገርበትን እርምጃ ዛሬ ‘ሀ’ ብሎ የሚጀምር መሆኑን አብስረዋል፡፡
አንበሳ ባንክ ቀጣዩን ዘመን ቀድሞ ለመኖር፣ አዲስን ነገር ለመቀመር፣ ከፍ ባለ እይታ ለመቅረብ የሚያስችል ቁመናን ተላብሶ ተለዋዋጭነት መገለጫው በሆነው የፋይናንስ ዘርፍ ባልተለመደ አካሄድ ለመራመድ የራሱን የሶስት ዓመት ፍኖተ ካርታ ቀርጿል፡፡
በዚህ አዲስ ፍኖተ ካርታ ባንኩ ለቀጣዮቹ ሶስት ዓመታት በኢንደስትሪው ውስጥ እንደ ናሙና እንዲታይ የሚያደረገውን፤ ለደንበኞቹ ብሎም ለሚያገለግለው ህብረተሰብ ፋይዳ ያለው የፋይናንስ አገልግሎት መስጠት የሚያስችለውን፣ ዘመኑን የሚገዛ የዲጂታል አገልግሎት ለማቅረብ የሚያበቃውን፣ በልዩ ልዩ አገልግሎቶቹም ፈጠራን ያማከለ ስራ ለመስራት የሚያስችለውን የስትራቴጂ አቅጣጫ ቀይሷል፡፡
በዚህ የባንኩን መጻኢ ገጽታ በሚተምነው ፍኖተ ካርታ በጊዜ ብዛት የማይሸረሸሩ፣ በሙሉ ልብ የተወጠኑ ዓላማ፣ ራዕይ፣ ተልዕኮ እና ዕሴቶች ተቀርጸዋል፡፡ እነዚህ መሰረታዊ እሳቤዎች ባንኩ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች፣ በደንበኛ አያያዝና መስተንግዶ፣ በሚሰራቸው የዕለት ተዕለት ተግባሮች፣ ለህበረተሰቡ ጥሪ በሚሰጠው ምላሽ፣ በአገራዊ እና ማህበራዊ እድገት ላይ በሚኖሩት ተሳትፎዎች አልፎም እንደ ባንክ በሚያደርጋቸው ሁለንተናዊ መስተጋብሮች የሚገለጡ ይሆናሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ እቅዶቹ በሙሉ በፋይናንስ ስነ ምግባር መርሆች ላይ የተንተራሱ በተለይም ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያዎች ተገዢ የሆኑ እና አዳዲስ የደንበኞችን ልምምድ ከፍ የሚያደርጉ ሆነው ተነድፈዋል፡፡
የአንበሳ ባንከ ፕሬዚደንት አቶ ዳንኤል ተከስተ ባደረጉት ንግግር ‘’በዛሬው ዕለት ይህን ወደ አዲስ ከፍታ የምናደርገውን ጉዞ የቃኘንበትን ስተራቴጂ በይፋ ወደ ስራ የምናስገባበት ብሎም የምንጀምርበት ቀን ነው’’ ያሉ ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞ የአንበሳ ባንክን ፍኖተ ካርታ ቀረጻ ላይ የተሳተፉ የስራ አመራር አባላትን እና ሰራተኞችን እውቅና ሰጥተዋል፡፡
የባንኩ የሶስት ዓመት ፍኖተ ካርታ በይፋ ወደ ስራ በገባበት በዚህ መርሃ ግብር ለዕቅዱ ዝግጅት አስተዋጽዖ ላበረከቱ ሰራተኞች የምስጋና የምስክር ወረቀት የተሰጠ ሲሆን የምስክር ወረቀቱንም ከአቶ ዳንኤል ተከስተ እጅ ተቀብለዋል፡፡

Leave A Comment