የአንበሳ ባንክ ሰራተኛ የሆኑት አቶ ሰይፈ ተስፋይ ካሕሳይ በ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ላመጡት ውጤት የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ እና የሥራ አመራር የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክቱን እያስተላለፈ አቶ ሰይፈ ተስፋይን የሚያበረታቱ ስጦታዎችን አበርክቷል፡፡በትግራይ ክልል ደቡባዊ ዞን ሰለዋ ወረዳ ደላ ከተማ በሚገኘው የአንበሳ ባንክ ቅርንጫፍ ላለፉት ሰባት አመታት በጥበቃ ስራ ላይ ተሰማርተው ሲሰሩ የነበሩት አቶ ሰይፈ ተስፋይ ካሕሳይ በ46 አመታቸው የ2018 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ተፈትነው 320.25 ነጥብ በማምጣት ወደ ዩንቨርስቲ በማለፋቸው የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ አባላት ፣ የሥራ አስፈጻሚ አባላት እና ሰራተኞች በሙሉ ደስታቸውን በተለያዩ መንገዶች ገልጸዋል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአንበሳ ባንክ ሥራ አመራር ከእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ባለፈ ለአቶ ሰይፈ ተስፋይ የሚከተሉትን ማበረታቻዎች ለማበርከት ውሳኔ አስተላልፏል፤
1ኛ. አቶ ሰይፈ ተስፋይ ካሕሳይ ወደ ዩንቨርሲቲ ለመግባት እና ለመማር የሚያስፈልጋቸው ማንኛውም ወጪ የዩንቨርስቲ ቆይታቸውን እስከሚያጠናቅቁ ድረስ ሙሉ ወጪያቸውን ባንኩ ይሸፍንላችዋል።
2ኛ. አቶ ሰይፈ ተስፋይ ካሕሳ ወደ ዩንቨርሲቲ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ አሁን የሚከፈላቸው ደመወዝ ሙሉ በሙሉ በየወሩ ለቤተሰቦቻቸው ይከፈላል፡፡
3ኛ. አቶ ሰይፈ ተስፋይ ካሕሳይ የዩንቨርሲቲ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ባንኩ በተገቢው የስራ ዘርፍ በመመደብ በቋሚነት ቀጥሮ የሚያሰራቸው ይሆናል።
አንበሳ ባንክ ህልምን የሚያቀጣጠል፣ ትልምን እውን የሚያደርግ እንዲሁም ወደ ግብ የሚደረገውን ጉዞ የሚያበረታ አጋር መሆን ብሎ የተነሳለትን ራዕዩን እንዲህ ያለውን ተነሳሽነት እና ቁርጠኝነት በመደገፍ የሚኖርለት መሆኑ ይህ ተግባሩ ማሳያ ሆኗል፡፡

Leave A Comment